ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የዓለምን ትኩረት እየሳበች ትገኛለች::

የግድቡ መሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን አስር አመት ያስቆጠረ ቢሆንም፤ ግድቡ በተለይ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በእጅጉ ሲያወዛግብ ቆይቷል::

ኢትዮጵያም የግድቡ ግንባታ ሀገራቱን በማይጎዳ መልኩ ሁሉንም የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በመግለጽ በግድቡ ዙሪያ ያላትን አቋም በየጊዜው ለሁሉም ለማሳወቅ ጥረት እያደረገች ትገኛለች::

ይሁን እንጂ ግብጽና ሱዳን በየጊዜው የተለያየ አቋም እያንጸባረቁ ባሉበት መገኘት እያቃታቸው ሀሳቦቸው ሲዋዥቅ ይስተዋላል::

ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ካከናወነችበት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ በተለየ መልኩ የተዘበራረቀ አቋማቸው እያንጸባረቁ ይገኛሉ ::

አሁን ላይ እነዚህ ሁለት ሀገራት በግድቡ ምክንያት ወዳጅነታቸውን ጠንከር ብሎ እየታየ ነው:: የግድቡን ግንባታ ሂደት ለማደናቀፍ በርካታ ጥረቶች ያደርጋሉ::

አበክረው የሚመክሩበትን ሀሳብ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማድረስ ተቀባይነት ለማግኘትና ተጽፅኖ ለመፍጠር የሚያደርጉት ገደብ የለሽ እሽቅድምድሞሽ ጉድ የሚያሰኝ ነው::

የህዳሴውን ግድብ ለደቂቃ እንኳን እንደማይቆም በተደጋጋሚ ያላትን አቋም ያሳወቀችው ኢትዮጵያ፤ የሀገርን ልዋላዊነት በማስቀደም የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በማከናወን፤

ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ለማከናወን ዝግጅቷን አጠናቃለች:: ታዲያ ይህንን የማይለወጥ አቋም መሆኑን ቀድመው የተረዱት እነዚህ ሀገራት ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ››

እንዲሉ ሆኖባቸው የራሳቸው ሀሳብና ፍላጎት ብቻ እንዲፈጸምላቸው ጽምፃቸው እንዲሰማ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥር ሲያስተጋቡ ቆይተዋል::

ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሳይጀመር ያለ የሌለ አቅማቸውንና ኃይላቸውን ተጠቅመው የውሃ ሙሌቱ እንዳይካሄድ ለማድረግ በእጅጉ ጥረት አድርገዋል::

ከትናንት በስቲያ ደግሞ ግብጽ የህዳሴው ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ፍላጎቷ ላይ ተጸእኖ እንደሌለው ስትናገር ተደምጣለች::

በዚህ አቋም የማትጸናዋ ግብጽ ነገ ሌላ አቋም ይዛ ብቅ ማለቷ አይቀሬ ነው :: እነዚህ አገራት በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ያለው አለመረጋገት ለስውር ዓላማቸው መጠቀሚያም ለማድረግ ሲሞክሩ ይስተዋላል::

የኢትዮጵያውያን አንድነት፤ ቅኝ ግዛትን ተጠይፎ የሀገራችንን ሉዓላዊነት አስጠብቆ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት የሚጠቀስ እንደሆነ መቼም ቢሆን የሚዘነጉት አይደለም::

ይህም ጠንቅቀው ስለሚያውቁም ነው ቀድመው አንድነታችን በመናድ በአጋጣሚው ለመጠቀም ያላቸውን ድብቅ ፍላጎት ለማሟላት የተሯሯጡት::

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን እዚህም እዚያም የሚከሰቱት ግጭቶችና ጥቃቶች ስንመለከት እነዚህ የውጭ ኃይሎች በእጅ አዙር የኢትዮጵያውያን አንድነት ለማፈራረስ ያለመ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም::

ሃይማኖትንና ከሃይማኖት፤ ብሔርን ከብሔር በማጋጨት እየተፈጸሙ ያሉ እኩይ ድርጊቶች የሀገር ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል አስልተው እየሰሩ ነው::

ይሁን እንጂ አላማቸው ምንም ይሁን ምን መቼ ቢሆን የምኞታቸው እንደማያሳካላቸው ቢያወቁም፤ ያለሙትን እስኪሳካላቸው የማይቆፍሩት ድንጋይ እንደማይኖር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል::

ሀገርን ለማፈራረስ አልመው ሲያሴሩ ከነበሩት የውስጥ ኃይሎች ጋር በማበር በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል አንድነታችን ለመናድ ጠንካራ ክንዳቸውን እያሳረፉብን እንደሆነም መታወቅ አለበት::

ለዓላማቸው ስኬት የወጠኑት ውጥን አንዱ ሳይሳካላቸው ሲቀር ሌላው አማራጭ እየተጠቀሙ በከንቱ ይደክማሉ :: እርስ በእርስ ለማጋጨት ከሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎች አንዱ የማህበራዊ ሚዲያ ፕሮፖጋንዳዎች ናቸው ::

በተለይ ግብፅ ከጅምሩ ጀምሮ ቢሆን የህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ያላት አቋም ‹ለእኔ ብቻ› የሚል አይነት ነበር::

የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ሲነሳ በእጅጉ ስለሚጨንቃት በየጊዜው ግድቡ ላይ ያነጣጠሩ ዘመቻዎች እያቀጣጣለች ትገኛለች ::

ለዚሁ ተግባር ብላ በመመልመል በአሰማራቻቸው የማህበራዊ ሚዲያ አካላት በእጇም፤ በእግሯ እየተራመደች ዘመቻውን ታካሂዳለች::

በቅርቡ እንኳን የፌስቡክ ኩባንያው መቀመጫቸውን ግብፅ ያደረጉ በህዳሴ ግድብ ላይ ያነጣጠሩ መልእክቶችን ሲያሰራጩ እንደነበር አስታውቋል::

በዚህ የተነሳ ኩባንያው 17 የፌስቡክ አካውንቶች፣ 6 ገጾች እና 3 የኢንስታግራም አካውንቶችን መዝጋቱን የሚታወስ ነው::

እነዚህ አካውንቶች ከ300 ሺህ በላይ ተከታዮች ነበሯቸው። ግርም የሚለው ደግሞ መልዕክቶቹ ይሰራጩ የነበረው በአማርኛ ቋንቋ መሆኑ ነው::

በእነዚህ አካውንቶች በአማርኛ ቋንቋ ይሠራጩ የነበሩት መልዕክቶች የህዳሴ ግድብ ላይ ያነጣጠረ እንደነበሩም ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ ጉዳይ ነው ::

በግብጽ ቅጥረኞች የአማርኛ ቋንቋን በመጠቀም የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ የሚያሰራጩ ስህተት የሆነ መረጃ ምን ያህል እኛን መስለው መቅረብና መከፋፈል እንደቻሉ ማሳያ ነው::

‹‹ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ››ማለት ይሄኔ ነው:: 

እኛን መስለው ለሀገራችን የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀበት የእያንዳንዳችን አሻራ ያረፈበት፤ የአንድነታችን መሠረት የሆነውን ግድባችንን ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ እያደረጉ መሆኑን መገንዘብ ይሻል::

በግድቡ ላይ የተከፈተው ዘመቻ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: በመካከላችን መቃቃር ፈጥረው ምንም ያህል ሊያራርቁን ቢሹ፤ በአባይ ጉዳይ ግን አንድ መሆናችን ማሳያ ጊዜው አሁን ነው::

ዛሬም አልረፈደብንም፤ ጊዜው ገና ነው:: በተነጣጠረብን ልክ እንኳን ባይሆን፤ ሃቅ ላይ ተመስርተን እውነት ይዘን ልንሞግት የማንቂያ ደውል እየጮኸ ነውና እንንቃ::

በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ቢሄድም ከሌሎች ሀገራት አንጻር ሲታይ በእጅጉ ኋላ ቀር እንደሆነ ይነገራል ፤

በተለይ አጠቃቀማችን ላይ ብዙ እንከኖች መኖራቸውን በየጊዜው ይገለጻል:: ለበጎ ተግባርና ለመልካም ሥራ የሚጠቀሙበት አካላት የመኖራቸውን ያህል በአንጻሩ ለጥላቻ፣

እርስ በእርስ ግጭት የሚሰብኩና ሀሰተኛ መልዕክቶችን ለማሰራጨት የሚጠቀሙበት አካላት መኖራቸውም እንዲሁ መታወቅ ያለበት ነው::

ለበጎ ተግባራት የሚጠቀሙት የተቸገሩ ወገኖቻቸውን እየረዱ ለወገን ደራሽነታቸው ያሳዩበት ነው::

በሀገር ተቆርቋሪ በመሆን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ለማድረግ ጠዋትና ማታ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚተጉ መኖራቸው መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ነው::

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ብልጽግና የማይሹ አካላት የለውጡን ጉዞ ለማደናቀፍ ይጥራሉ:: ደስ ሲላቸው የህዳሴ ግድብ ግንባታ፤ የውስጥ ጉዳዮች በተመለከተ ምክንያቶችን እየደረደሩ ተጽፅኖ ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ::

ለዚህም የሰሞኑ አሜሪካና አውሮፓዊያኑ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉት ጫና ማንሳት ይቻላል::

ይህ ለመመከት የሚያስችለንን ስንቅ ይዘን መቃወም ይጠበቅበናል:: ይህ የመንግሥት ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ ነው::

የሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለውን ነባራዊ እውነታና ሃቅ ለዓለም ለማስገንዘብ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ መወጣት ይኖርባቸዋል::

Please Share for your Friends

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on whatsapp