ቪሳት /VSAT/ ቴክኖሎጂ ምንድን ነው? (የምርጫ ታዛቢ ቡድኑ ይዤ ካልገባሁ የሚለው ቪሳት)

የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉልኝ የ2013 ዓ.ም አጠቃላይ አገራዊ ምርጫን ለመታዘብ ወደ ኢትዮጵያ አልመጣም ማለቱን የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን በሰጠው ሳምታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።

የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ ቅድሚያ መግለጫ የመስጠቱ መብት የኔ ሊሆን ይገባል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ VSAT የተባለ የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ይዤ መግባት እፈልጋለሁ የሚለው ነው፡፡

ለመሆኑ ቪሳት /VSAT, Very Small Aperture Terminal/ ምንድን ነው?

ቪሳት ልክ እንደ ዲያላፕ፣ ብሮድባንድ እና እንደሌሎች ሁሉ ኢንተርኔት ማግኘት የሚያስችለን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ልዩነቱ ቪሳት ቴክኖሎጂ በቀጥታ ለተጠቃሚው ያለሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የሳተላይት ኢንተርኔት አገልግሎትን ማስገኘት መቻሉ ነው፡፡ እንደየአገራቱ የቴሌኮምና ህግና የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶች ቢለያይም ይህን ቴክኖሎጂ ያለመንግስትና ያለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እውቅናና ፈቃድ ማንኛውም ግለሰብ እንዲሁ ቤቱ አምጥቶ በመገጣጠም የሚጠቀምበት ቀላል ነገር አይደለም፡፡

እስኪ ነገርየውን በደንብ እንመልከተው …

ኔትወርክ ኦፕሬቲንግ ሴንተር እና ቴሌፖርትን እንደአገናኝ በመጠቀም ሕዋ /space/ ላይ የሚገኙ ሳተላይቶችን መሬት ላይ ከሚገኙ ተጠቃሚዎች ጋር በዲሽ ወይንም በአንቴና አማካኝነት በማገናኘት ከአካባቢው የቴሌኮም ባለስልጣን ቁጥጥር ውጪ አልያም በላላ ቁጥጥር ውስጥ ሆነው የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል፡፡ እንግዲህ ይህ ቴክኖሎጂ ነው ቪሳት /VSAT/ ተብሎ የሚጠራው፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ ከመረጃ ጥበቃ አንፃር ምን አልባት ከዋናው የኢንተርኔት መሰረተ ልማት /Infrastructure/ የወጣ ራሱን የቻለ በቀጥታ ከተጠቃሚው ጋር ብቻ ግንኙነት የሚፈጥር ሊሆን ስለሚችል ምን አልባት የቁጥጥር ሁኔታው /Control feature/ አነስ ሊል የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ተብሎ ይታሰባል።

የቪሳት /VSAT/ አይነቶች

 • ተንቀሳቃሽ ቪሳት /VSAT/

እነዚህ ልክ መኪና በምርት ስም፣ በክብደት፣ በወንበር መጠን ዋጋው እንደሚለያየው ሁሉ በሚሰጡት ግልጋሎትና ጥራት ዋጋቸውም በዚያን ያክል ከፍተኛ ልዩነት ሊያሳይ ይችላል፡፡ ይህ ቪሳት የአንቴናው ርዝመት በጨመረ ቁጥር አልያም የሳህኑ ስፋት ከፍ ባለ ቁጥር ዋጋውመ በዚያው ልክ ይጨምራል፡፡

ከሚሰጡት አገልግሎቶች መካከል

 • የርቀት ትምህርት
 • ደህንነቱ የተጠበቀ ግላዊ የድምፅ ጥሪ ማድረግ
 • ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት

 • የባህር ኃይል ቪሳት /VSAT/

እነዚህ በመርከቦች ላይ የሚገጠሙ የቪሳት አይነቶች ደግሞ መርከቡ የቱንም ያክል ቢናወጥ አንቴናው ከሳተላይቱ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት እንዳያውከው በተፈለገው አቅጣጫ እንደልብ መንቀሳቀስ በሚያስችለው መንገድ ይገጠማሉ፡፡ እንደንፋስና ሌሎች ምክንያቶች ስራቸውን እንዳያስተጓጉሉት ከፋይበር መስታወት በተሰራ ቤት አልያም መጠበቂያ ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡

ከሚሰጡት አገልግሎቶች መካከል

 • የባህር ላይ ወንበዴዎችን ማሰስ እና መከላከል
 • በመርከቡ ላይ ለሚገኙ ተጓዦችና ሰራተኞች ፈጣን የመረጃ ልውውጥን ማስገኘት
 • በአለም ላይ በሚገኙ ባህሮች ላይ የሚደረጉ ጉዞዎችን ደህንነት ማረጋገጥ
 • በዋናው ቢሮ፣ በመቆጣጠሪያ ኮንሶል እንዲሁም በመርከቦች መካከል የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ማስቻል
 • መርከቦች የሚገኙበትን ቦታ በትክክል ማመላከት
 • የመርከቦች መሳሪያዎች ሥራን በርቀት መቆጣጠር

 • በተሽከርካሪ ላይ የሚገጠም ቪሳት /VSAT/

ርዝመታቸው ከ 75 ሳንቲሜት እስከ 1 ሜትር ከ20 ሳንቲሜትር ይደርሳሉ፡፡ እነዚህ በአብዛኛው በተሽከርካሪዎች ጣሪያ ላይ የሚገጠሙት ቪሳቶች በተተከሉ በደቂቃዎች ውስጥ በመኪናው ውስጥ በተገጠመው የሳተላይት ግንኙነት መሳሪያ ጋር በመጣመር ወዲያውኑ ስራቸውን መጀመር ይችላሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል በድንገተኛ ጊዜዎች ለፈጣን የመረጃ ልውውጥ ተመራጭ ሆነው የተገኙት

ከሚሰጡት አገልግሎቶች መካከል

 • የድምፅና የምስል አገልግሎት
 • የቀጥታ የዜና ዘገባዎች

 • በቋሚ ቦታ ላይ የተወሰነ ቪሳት /VSAT/

በመደበኛው መንገድ የኢንተርኔት አገልግሎትን ማድረስ በማይቻልባቸው አካባቢዎች የብሮድባንድ ኢንተርኔትን ለማደረስ በጣም ተመራጭ የቪሳት አይነት ሲሆን የተስተካከለ የ VSAT አንቴና ለደቡባዊ ሰማይ ግልፅ እይታ ባለው ቦታ ላይ መትከል እስከቻለ ድረስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ኢንተርኔት ማግኘት ያስችላል፡፡

Please Share for your Friends

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on whatsapp