የጥፍር ፈንገስ (nail fungus) ምንድነው፣ እንዴትስ መከላከል ይቻላል?

የጥፍር ፈንገስ የእጅ ጣት ጥፍራችንን አሊያም የእግር ጣት ጥፍራችንን ሊያጠቃ የሚችል የተለመደ የጤና እክል ነው። ጥፍር በፈንገስ ሲጠቃ የተፈጥሮ ቀለሙን እያጣ ይሄድና ወደ መበስበስና መፈርፈር ይደርሳል። ይህ አይነቱ የጤና እክል አንዱ የጣታችን ጥፍር ላይ ከተከሰተ ወደሌሎች ጣቶች በቀላሉ ሊዛመት ይችላል። ይህ ዓይነቱ የጥፍር በሽታ በህክምናው መጠሪያው Onychomycosis በመባል የሚታወቅ ነው።

የጥፍር ፈንገስ በአብዛኛው በእግር ጣት ጥፍሮች ላይ የሚከሰት ቢሆንም፣ በእጃችን ጣቶች ላይም የመከሰት እድል አለው። በጥፍር ፈንገስ መጣቃታችንን ለማወቅ የሚከተሉትን ምልክቶች ልብ ማለት ያስፈልጋል…

 1. የጥፍር መደደር
 2. የጥፍር የተፈጥሮ ቀለሙን ማጣት(መንጣት ወይም መወየብ)
 3. የጥፍር ቅርጽ መቀየር
 4. የጥፍር የጠረን ለውጥ እና
 5. የጥፍር መጥቆር ናቸው።

ቅድመ መከላከል

የተለያዩ የጥንቃቄ መንገዶችን በመከተል የጥፍር ፈንገስ በሽታን መከላከል ይቻላል። የህክምና ባለሞያዎች ከሚመክሩት የጥንቃቄ መንገዶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

 1. እጅና እግርን ማጽፋት (መታጠብ)
 2. ጥፍራችንን በአግባቡ አስተካክሎ መቁረጥ
 3. የጥፍር መቁረጫችንን በየጊዜው በሚገባ ማጽዳት
 4. የማያልብ ካልሲ ማድረግና ቶሎ ቶሎ መቀየር፣ ካልሲዎቻችንን ቶሎ ቶሎ ማጽዳት
 5. የጥፍር ቀለምና አርቲፊሻል ጥፍሮችን አዘውትሮ አለመጠቀም
 6. በባዶ እግር እርጥበታማ መሬት ላይ አለመሄድ

አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

ሰዎች ለጥፍር ፈንገስ በተለያየ መንገድ ሊጋለጡ ይችላሉ። በሽታው ያን ያክል ለጤና አስጊ ባይሆንም አንዳንድ ሁኔታዎች በሽታውን ሊያባብሱት ይችላሉ። ከነዚህም መካከል…

 1. የስኳር ህመም
 2. እድሜ (ከ65 አመት በላይ)
 3. አርቲፊሻል ጥፍር አዘውትሮ መጠቀም
 4. ብዙ ሰዎች በጋራ የሚጠቀሙበት ገንዳ ውስጥ መዋኘት
 5. የተዳከመ በሽታን የመከላከል ስረዓት
 6. የጥፍር ለረዥም ጊዜ ለእርጥበት መጋለጥ

 

 

Please Share for your Friends

Share on facebook
Share on telegram
Share on twitter
Share on linkedin
Share on whatsapp